አዲሱ የብር ኖት ቅየራ በዛሬው ዕለት፣ መስከረም 6/2012 ዓ.ም ከሰዓት መጀመሩን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ አቶ አልሰን አሰፋ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
በዝግጅቱ ላይም የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ የተገኙ ሲሆን፤ ዛሬ ከቀኑ 9፡30 ጀምሮም በአዲስ አበባ አካባቢ ባሉ ባንኮች ብር መቀየር ተጀምሯል ብለዋል ሥራ አስኪያጁ።
በመሆኑም የብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው መመሪያ መሠረት፤ 100 ሺህ ብር እና ከዚያ በላይ ገንዘብ በእጃቸው ላይ ያለ ግለሰቦችና አካላት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ወደ ባንክ በመሄድ ገንዘቡን መቀየር እንደሚችሉም አቶ አልሰን ገልፀዋል።
አገልግሎቱ በማንኛውም የባንክ ቅርንጫፍ እንደሚሰጥ የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፤ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች እጃቸው ላይ ያለውን ብር ወደ አዲሱ መቀየር አሊያም ከሒሳብ ቁጥራቸው አዲሱን የብር ኖት ማውጣት እንደሚችሉ ተናግረዋል።
እጃቸው ላይ ከ100 ሺህ ብር በታች ያላቸው ግለሰቦችም እስከ 2 ወር ከግማሽ ድረስ ገንዘባቸው እንዲቀይሩ ቀነ ገደብ ተቀምጧል ብለዋል።
ከ100 ሺህ ብር በላይ ያላቸው ግን በዚህ አንድ ወር ብቻ ቅየራውን ማጠናቀቅ ያለባቸው ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ የሚመጣ በየትኛውም ባንክ እንደማይስተናገድ ሥራ አስኪያጁ አስጠንቅቀዋል።
በመሆኑም በዚህ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን ከኮሮና በመጠበቅ እጃቸው ላይ ገንዘባቸው በአዲሱ የብር ኖት እንዲለውጡ አሳስበዋል።
ከዚያ በታች የገንዘብ መጠን ያላቸው ሰዎች የተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እስከ ሁለት ወር ከግማሽ ቢሆንም በዚህ ወር ውስጥም ግን መቀየር እንደሚችሉ አቶ አልሰን ጠቁመዋል።
10 ሺህ እና ከዚያ በላይ እጃቸው ላይ ያለ ሰዎች ደግሞ ገንዘባቸው አካውንታቸው ላይ ማስገባት የሚጠበቅባቸው ሲሆን የሒሳብ ቁጥር ከሌላቸውም መታወቂያ እና ጉርድ ፎቶግራፍ በመያዝ የሒሳብ ቁጥር ከፍተው ገንዘባቸው እዚያ ማስቀመጥ ይችላሉም ተብሏል።
በተቀመጠው ጊዜም ከባንክ ውጪ የሚገኙ ገንዘቦች የሚሰበሰቡበት ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንም ሥራ አስኪያጁ አክለዋል።
አቶ አልሰን እንዳሉት ገንዘቡን ለመሰብሰብ የተሰጠው አጠቃላይ ጊዜ ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ሦስት ወራት ውስጥ ነው።
በዚህ ጊዜም ከባንክ ውጭ አለ ተብሎ የሚገመተው ወደ 113 ቢሊየን ብር ወደ ባንክ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ኃላፊው ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ኢትዮጵያ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ስትገለገልባቸው የነበሩ የ10፣ የ50 እና የ100 የገንዘብ ኖቶችን ሙሉ ለሙሉ ለመተካት አዲስ የገንዘብ ኖቶችን ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።
ከአዲሶቹ የገንዘብ ኖቶች ውስጥም በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የባለ ሁለት መቶ ብር ኖትም አሳትማለች።
አገሪቷ ነባሮቹን የብር ኖቶች ለመቀየር ሌላ ወጪን ሳይጨምር ለህትመት ብቻ 3.7 ቢሊየን ብር ማውጣቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አስታውቀዋል።