“ብር ቅያሬውን በተመለከተ የደረሰን የተሟላ መረጃ የለም”-የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር ማህበሩ ከአሁን ቀደም ከባንክ ውጭ ይዘዋወራል ያለው 113 ቢሊዬን ብር ወደ ባንክ እንዲመለስ የብር ቅያሬን ጭምር በምክረሃሳብነት ማቅረቡ የሚታወስ ነው

“ብር ቅያሬውን በተመለከተ የደረሰን የተሟላ መረጃ የለም”-የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር ማህበሩ ከአሁን ቀደም ከባንክ ውጭ ይዘዋወራል ያለው 113 ቢሊዬን ብር ወደ ባንክ እንዲመለስ የብር ቅያሬን ጭምር በምክረሃሳብነት ማቅረቡ የሚታወስ ነው
Sep 15, 2020

ብር ቅያሬውን በተመለከተ የደረሰን የተሟላ መረጃ የለም”-የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዛሬው ዕለት ያስታወቁትን የግብይት ገንዘብ ዓይነቶች ለውጥን በተመለከተ የደረሰው መረጃ እንደሌለ የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር (Ethiopian Bankers Association) አስታወቀ፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ በርከት ያሉ ጥያቄዎች ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ቀርበውልናል ያሉት የማህበሩ ጽህፈት ቤት ተጠባባቂ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ግርማ በይፋ የደረሰን ነገር የለም፡፡ የተሟላ መረጃም እያገኘን አይደለም፡፡ ስለፋይዳና ተጽዕኖው ልንናገርም አንችልም ሲሉ በተለይ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል የብር ለውጡን በተመለከተ በዚህ ሳምንት ሊሰጡ የሚችሉት መግለጫ እንደሚኖር በመጠቆም፡፡

ማህበሩ የሃገሪቱ ባንኮች ገጥሟቸዋል ያለውን የገንዘብ እጥረት (ሊኩዲቲ) ችግር በተመለከተ ከወራት በፊት መግለጫን ሰጥቶ ነበር፡፡

በመግለጫው የችግሩ ምንጮች ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች ያስቀመጠ ሲሆን ብሄራዊ ባንክ ሊወስዳቸው ይገባል ያላቸውንም ምክረ ሃሳቦችን አቅርቧል፡፡

ለገጠመው ችግር መንስዔ ናቸው ከተባሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ከፋይናንስ ተቋማት ውጭ ይዘዋወራል የተባለው ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ነበር፡፡

5 ዓመታት በፊት ማለትም .. 2016 ከባንክ ውጭ ሲዘዋወር የነበረው 63 ቢሊዬን ጥሬ ብር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት (2020) 113 ቢሊዬን ብር ደርሷል ሲልም ነበር ማህበሩ በመግለጫው ያስታወቀው፡፡

ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወደ ፋይናንስ ተቋማቱ የሚመለሰው ብርን በመቀየር እንደሆነና ጥያቄው ይመለሳል ብሎ እንደሚጠብቅም በወቅቱ አስታውቆ ነበር፡፡

ይህን በመጥቀስ ማህበሩ ከአሁን ቀደም ስለ ብር ቅያሬ ጠይቆ እንደነበር አል ዐይን ላቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ኤርሚያስ ምክረ ሃሳቡን አቀረብን እንጂ የመገበያያ የብር ኖቶችን በተመለከተ ያልነው ነገር የለም ሲሉ መልሰዋል፡፡

አንዱ ያቀረብነው ምክረ ሃሳብ ብሄራዊ ባንክ የራሱን እርምጃ ቢወስድ፤ በረጅም ጊዜ ደግሞ ብር ቢቀየር የሚል ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ግን ብሄራዊ ባንክ ራሳችን ያከማቸነውን ገንዘብ እንዲሰጠን የሚል ነበር፡፡ ለዚህም 15 ቢሊዬን ብር ተለቀቀ፡፡ ስለዚህ የዛን ጊዜ የነበረው ችግር የብር መጠኑ ላይ እጥረቱን የማስቀረት እንጂ ኖቱ ላይ አልነበረም፡፡ ይሄ ኖት ይደረግ ይሄ ይሁን መቶ ብር ይሁን 500 ብር ይሁን የሚል አንድም ነገር ግን አላልንም ሲሉም ነው የሚያስቀምጡት፡፡

ጉዳዩ ለእኛም አዲስ ነገር ነው የሚሉም ሲሆን የሚቀየረው ብር በምን ያህል ጊዜ  ሲስተም ይወጣል? በምን ያህል ጊዜስ ሊሰበሰብ ይችላል? ምን ያህል ተጽዕኖ አለው? ያልተቀየሩ የገንዘብ ኖቶችን በተመለከተስ? የሚለውን ገና ማየት አለብን በመላ ምት ልንናገር አንችልም በሚል ስለ ጉዳዩ አብራርተዋል፡፡

መንግሥት አዳዲስ የደህንነት ገጽታዎች እና ሌሎችም መለያዎች የተካተቱባቸው የገንዘብ ዓይነቶችን ለግብይት እንደሚያውል ዛሬ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

ነባሮቹ 10 50 እና 100 ብር የገንዘብ ዓይነቶች ሙሉ ለሙሉ የሚተኩ ይሆናል የተባለም ሲሆን አዲስ 200 ብር ኖት በተጨማሪነት ግልጋሎት ላይ እንደሚውል፣የ5 ብር ገንዘብ ባለበት ቀጥሎ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ሣንቲም እንደሚለወጥ መገለጹም አይዘነጋም።

የገንዘብ ቅያሬው መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንዲሁም ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ የሚዘዋወረውን ገንዘብ ለመሰብሰብ፣ ሙስናን እና የኮንትሮባንድ ሥራዎችን ለመቀልበስ ያለመ፣ የፋይናንስ ተቋማትን የገንዘብ እጥረት ለመቋቋም እንደሚያስችልም ተገልጿል፡፡