ኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር ገቢና ወጪ ዕቃዎችን በማጓጓዝ ውጤታማ መሆኑን አስታወቀ

ኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር ገቢና ወጪ ዕቃዎችን በማጓጓዝ ውጤታማ መሆኑን አስታወቀ
Sep 20, 2020

የግንባታ ሒደቱን በአምስት ዓመታት ውስጥ አጠናቆ ... በጥር ወር 2018 የገቢና የወጪ ንግድ የጭነት አገልግሎት መጀመሩን፣ ያለ ምንም ችግር መንቀሳቀስ መቻሉንና ውጤታማ ሥራ ማከናወኑን የኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማኅበር አስታወቀ፡፡

ማኅበሩ ዓርብ መስከረም 8 ቀን 2012 .. ላለፉት አንድ ሺሕ ቀናት ስለሰጠውና እየሰጠ ላለው የጭነት አገልግሎት፣ እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ስለመጣው የሦስቱ አገሮች ማለትም የኢትዮጵያ፣ የጂቡቲና የቻይና ግንኙነትን አስመልክቶ ፉሪ ለቡ በሚገኘው የፕሮጀክት ቢሮው እንዳስታወቀው፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት 588 የጭነት ባቡሮች፣ 38,000 ኮንቴይነሮች፣ 730 ሺሕ ቶን ዕቃዎች፣ 73,000 ቶን ማዳበሪያና 60,000 የጥራጥሬ እህሎች ማጓጓዝ መቻሉን የሲሲኢሲሲ ዋና ሥራ አስኪያጅና የሲሲኢሲሲና ሲአርኢሲ የጋራ ፕሮጀክት ቢሮ ተወካይ ሚስተር ጉዎ ቾንግ ፈንግ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለብዙ ሺሕ ኢትዮጵያውያንና ጂቡቲያውያን የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግር መፈጠሩን ያስታወሱት ተወካዩ፣ የወጪና የገቢ ዕቃዎችን በማጓጓዝ ... 2018 እስከ 2019 ዓመታዊ ገቢው 45 በመቶ የነበረ ቢሆንም ... 2020 ግማሽ ዓመት ድረስ ከቀድሞው ጋር ሲነፃፀር 51 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ይኼ የሆነው የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱ በታወቀበትና የዓለም ሁሉ ቀውስ በሆነበት ጊዜ ውስጥ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የጭነት አገልግሎቱ በተለይ የአርሶ አደሩን ምርት በወቅቱ ወደሚፈለገው የገበያ መዳረሻ ወቅቱን ጠብቆ እንዲደርስ በማድረግ፣ የአኗኗር ዘይቤውንም እንዲያሻሽል ዕገዛ ማድረጉን አክለዋል፡፡

የባቡር ትራንስፖርት በመጀመሩ በተለይ የንግዱ ማኅበረሰብ ምርጫው የባቡር ትራንስፖርት እንዲሆን እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ሚስተር ፈንግ፣ በዓመቱ ውስጥ የተገኘው ገቢም ለዚህ ምስክር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተወካዩ ስለፕሮጀክቱ አጀማመር፣ ስለግንባታውና ወደፊት ስለታሰበው ፕላን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ የቻይና ማኔጂንግ ኮንትራክተር ከኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር ጋር በመሆንና በኢትዮጵያ መንግሥት አመራር ሰጪነት፣ ... ኅዳር 2020 በቀን ውስጥ የነበረውን ሁለት ምልልስ ወደ አራት ከፍ እንደሚያደርጉ፣ በዚህም 2021 እስከ 2022 ባሉት ዓመታት በቀን 280 ሺሕ ዶላር ወይም በዓመት 100 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ... 2023 ምልልሱን ወደ ስድስት ከፍ በማድረግ ገቢውንም በዓመት ወደ 150 ሚሊዮን ዶላር ለማድረስ ዕቅድ መያዙንም አክለዋል፡፡

በወጪና በገቢ የጭነት አገልግሎት በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ መሆኑን ለማሳወቅና በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ስንብትን አስመልቶ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ የተገኙት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ / ዳግማዊ ሞገስ እንደገለጹት፣ ኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር ‹‹በቅርቡ ሙሉ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አሁን ካየሁት ሁኔታ ምስክር መሆን እችላለሁ፤›› ብለዋል፡፡ የቻይና ሕዝብና መንግሥት ይኼን ትርጉም ያለው የባቡር ሐዲድ በተሳካ ሁኔታ ማከናወናቸውን ጠቁመው አመሥግነዋል፡፡ ከግንባታው ጀምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት የጀመረው የጭነት አገልግሎት በፍጥነት የተተገበረበትና ያስገኘው ውጤት እንዳስደሰታቸው የገለጹት ሚኒስትሯ የሥራው ክንውን የኢትዮጵያን፣ የጂቡቲንና የቻይናን የረዥም ጊዜ ግንኙነት ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ እስከ ጂቡቲ የተዘረጋውን 756 ኪሎ ሜትር የባቡር ሐዲድ፣ ... 2012 ግንባታውን ጀምሮና አጠናቆ 2018 ደግሞ የጭነት አገልግሎት ሥራ መጀመሩ የሚያስመሠግነው መሆኑንና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውም እንደ ተቆጣጣሪ አካል፣ በቅርብ በመከታተልና በመቆጣጠር ለፕሮጀክቱ መሳካት ዕገዛ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡ ይኼ ግዙፍ ኢንቨስትመንት መሆኑንና ለሦስቱ አገሮችም ትርጉም ያለው ሥራ መሆኑንም አክለዋል፡፡ የባቡር ግንባታ ፕሮጀክት ግዙፍ ከመሆኑ አንፃር ተግዳሮቱም ከፍተኛ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሯ፣ ተግዳሮቶችን ለመወጣት በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ሚስተር ታን ጂያን ያደረጉላቸው ዕገዛ ከፍተኛና ትርጉም ያለው መሆኑን ጠቅሰው አመሥግነዋል፡፡ ተልዕኳቸውን ጨርሰው የተሰናበቱ ቢሆንም፣ በፕሮጀክቱ ሲታወሱ እንደሚኖሩም አክለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የአገሪቱን የረዥም ጊዜ ግንኙነት ከፍ ባለ ሁኔታ ከማስቀጠሉም በተጨማሪ የቴክኖሎጂ ሽግግር መፍጠር መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡ የሎጂስቲክስ አገልግሎት በመስጠት ከኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር ጋር በቅርበት የሚሠራውን የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትና ሌሎችን የሎጂስቲክስ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችን አመሥግነው፣ እንቅስቃሴው ሌሎች ደንበኞችም እንዲጠቀሙ የሚገፋፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዓለም ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ 13 አገሮች የሕዝባቸው ብዛት 100 ሚሊዮን የሚበልጥ ሲሆን፣ ከእነዚህ አገሮች ውስጥ የባህር በር የሌላት ኢትዮጵያ ብቻ መሆኗን የተናገሩት ተሰናባቹ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ሚስተር ታን ጂያን ሲሆኑ፣ ይኼ ለዕድገቱ ማነቆ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይኼ የባቡር ሐዲድ ግንባታ ፕሮጀክት ከባሕር በር ዝግነት ወደ የብስ ግንኙነት የቀየረ ፕሮጀክት መሆኑን አክለዋል፡፡ ይኼም የባቡር ትራንስፖርት መስጫ መስመር ብቻ ሳይሆን የሕይወት መንገድ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለመሆን እየጣረች መሆኑን የጠቆሙት ሚስተር ጂያን፣ ከገነባቻቸው 15 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ዘጠኙ በኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመር ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ ይኼም፣ ‹‹ኢንዱስትሪያላይዜሽን ይባላል፤›› ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል በምድር ባቡር ማቆሚያ ቦታዎች የሪል ስቴት ግንባታ እየተካሄደና የከተሞች መስፋፋት እየታየ መሆኑን ጠቁመው፣ የባቡር ትራንስፖርት መስመር ብቻ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ ቀበቶና የልማት ኮሪደር በመሆን የኢኮኖሚ ዕድገት እያመጣ ያለ ፕሮጀክት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮ ጂቡቲ የጭነት አገልግሎት መጀመሩና ውጤታማ መሆን መቻሉ ለሦስቱም አገሮት ትልቅ ስኬት እንደሆነ የገለጹት አምባሳደሩ፣ ወደፊት ሊሠራ በታቀደው መሠረት በቀን አራት ጊዜ ምልልስ በማድረግ ቢያንስ ቢያንስ ኪሳራ የማይመዘገብበት አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ቀስ በቀስም ትርፍ ማስመዝገብ እንደሚቻል የፀና እምነት እንዳላቸውም አክለዋል፡፡ ኢትዮጵያና ቻይና 2018 ባደረጉት ብድርን የማስተካከል ስምምነት፣ የባቡር ፕሮጀክቱን ቀጣይ ሥራ በዘላቂነት ለመሥራት መንገድ የጠረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በአጠቃላይ መንግሥት፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ሲሲኢሲሲ እና ሲአርኢሲ ተደጋግፈውና ተመካክረው የኢትዮጵያን ልማት ማፋጠን እንዳለባቸው ተሰናባቹ አምባሳደር ታን ጂያን አሳስበዋል፡፡

የሕዝብ ትራንስፖርቱ በጥሩ ሁኔታ ቀጥሎ ሳለ የኮሮና ወረርሽን በመከሰቱ መቆሙንና የጭነት ትራንስፖርት መቀጠሉን የገለጹት የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ሰርካ፣ የሕዝብ ትራንስፖርትም በቅርቡ እንደሚጀምርም አስታውቀዋል፡፡ የጭነት ትራንስፖርት ግን በአመርቂ ሁኔታ መቀጠሉን አክለዋል፡፡ ዝቅ ባለ የትራንስፖርት ክፍያና በፈጠነ ጊዜ አገልግሎቱን ስለሚሰጥ የደንበኛ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡